መታወቂያ ገጽየቫቲካን ሬድዮ
የቫቲካን ሬድዮ   
more languages  

     መታወቂያ ገጽ > ቤተ ክርስቲያን >  2013-03-30 10:45:31
A+ A- ገጹን ለማተምዘደብረ ዘይትየዐቢይ ፆም አምስተኛ ሳምንት
«እግዚአብሔር ገሀድ ይመጽዕ፤ወአምላክነሂ ኢያረምም፤እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡» (እግዚአብሔር ግልጽ ሆኖ ይመጣል፤አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤እሳት በፊቱ ይነዳል)፡፡ መዝ. 49(50)፡3፡፡ RealAudioMP3
ዛሬ የምንገኝበት አምስተኛው የዐቢይ ፆም ሰንበት «ደብረ ዘይት» ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ቀን የሚነበበው ወንጌል (ማቴ 24፡1-36) ስለ ዓለም መጨረሻ እና ከዛም በፊት ስለሚሆኑት ነገር ይናገራል፡፡ ይህን በተመለከተ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ብዙ ምልክቶችን ነገራቸው፤ የጦርነት ወሬ ይሰማል፣ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሳል፣ረሃብ፣ ድርቅ፣ቸነፈር፣ የምድር መናወጥ ይሆናል፣ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፣በስሜ ይመጣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ…«ከዓመጻ ብዛት ከክፋትም መግነን የተነሳ የብዙዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡» (ማቴ 24፡12)፡፡ የዛሬው አስተምሕሮም ትኩረቱን በዚህ ላይ ያደረገ ነው፡፡
በእምነት ያልጠነከሩ እና የዋህ ሰዎች እነዚህ ነገሮች ተከስተዋል እየተከሰቱም ነው ነገር ግን ክርስቶስ አልመጣም የሚል አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ክርሰቶስ እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱ እኔም አብሬ እመጣለሁ አላለም፤ ወንጌሉ «ይህ ሁሉ የጭንቅ መጀመሪያ ነው» እንዲሁም «ስለዚያች ቀን እና ሰዓት የሚያውቅ የለም» ነው የሚለው (ማቴ 24፡8፣36)፡፡ የሚሆኑት ነገሮች አስቀድመው ስለተነገሩን ዕድለኞች ነን፡፡ ስለዚያች ቀን መምጣት በተመለከተ ግን ሰው ሊቸኩል አይገባውም፣ መዘግየቱ ለጥቅማችን ነውና፡፡ ቅ. ጴጥሮስ እንዲህ ነው የሚለው «አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው የተስፋ ጌታ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፡፡ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ፣ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ ስለናንተ ይታገሳል» (1ጴጥ 3፡9)፡፡
በተፈጥሮ ከሚደረሱት አደጋዎች በስተቀር ሌሎቹን በገዛ እጃችን የምናመጣቸው ናቸው፡፡ ፍቅራችን ለብ ያለ ወይም የቀዘቀዘ ሲሆን ወይም ከነጭራሹ ሲጠፋ የእግዚአብሔርን ቁጣ እንቀሰቅሳለን፡፡ ሰው በገዛ ወላጆቹ ላይ ይሸፍታል፣ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሳሳል፣በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ እርስ በእርስ በመጣላት ሕይወት እስከማጥፋት ይደርሳሉ፡፡ እስቲ ዘመናችንን ልብ ብለን እንመልከት፣ «እኔ፣ለእኔና የእኔ» የሚል መንፈስ እየገነነ የመጣ አይመስላችሁም? እንግዲህ የቀዘቀዘ ፍቅርን በመንፈስ ቅዱስ፣በቃለ እግዚአብሔር፣በምስጢራት እንዲሞቅ ማድረግ ነው የሚጠበቅብን፡፡ መጨረሻው መቼ ይሆን ብሎ ከመጨነቅም ያ ቀን ሲመጣ በጌታዬ ፊት ምን ይዤ እቀርባለሁ የሚለው ጥያቄ ነው ሊያሳስበን የሚገባው፡፡
አዎን በምድራችን ላይ ጦርነቱ፣አለመግባባቱ፣ክፋቱ…የበዛው ባለራዕዩ ቅ. ዮሓንስ እንዳለው የቀደመውን ፍቅራችንን፣ንጹህ አምልኳችንን…ስለተውነው ነው፤ ዮሐንስ መፍትሔውንም አብሮ ይጠቁመናል «ከወዴት እንደወደቅህ ተመልከት፣ንስሐም ግባ» (ራዕ. 3፡4-5)፡፡…
የተሰጡን ምልከታዎች ሊያስፈሩን አይገባም፣መጽናት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ትንሣኤ ያለው ሁሌም ከጎለጎታ በኋላ ነው፤እዚያ ደረጃ ላይ የሚደረሰው ደግሞ እስከመጨረሻ የሚጸና ብቻ ነው (ማቴ 24፡13)፡፡ ቸሩ አምላካችን የነፍስ ትዕግስትን አብዝቶ ይስጠን፡፡ አሜን፡፡

ሰላም ወሠናይ
አባ ዳዊት ወርቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን
Share


ማን መሆናችን የዝግቶቹ ሰዓታት ለዝግጅት ክፍል ይጻፉ የቫቲካን ሬድዮ ክንውን ማገናኛዎች ሌሎች ቋንቋዎች የቫቲካን መታወቂያ ገጽ ሃገረ ቫቲካን የር.ሊ.ጳ. ሊጡርጊያውያን ሥርዓታት
የዚህ ድረገጽ ይዞታዎች ደራሲ መብት የተጠበቀ ነው ©. ድረ መስተዳድር / የደራሲያን ስሞች / ሕጋዊ ሁኔታዎች / ማታወቂያ