መታወቂያ ገጽየቫቲካን ሬድዮ
የቫቲካን ሬድዮ   
more languages  

     መታወቂያ ገጽ > ቤተ ክርስቲያን >  2013-06-01 12:16:08
A+ A- ገጹን ለማተምየትንሣኤ አምስተኛ ሰንበት«መረቡን በታንኳው በስተቀኝ ጣሉ ዓሣም ታገኛላችሁ» (ዮሐ. 21፡6)፡፡ RealAudioMP3 በዚህ የወንጌል ክፍል (ዮሐ. 21፡1-14) ሐዋርያቱ በጴጥሮስ መሪነት ወደ ቀድሞው ሥራቸው እንደተሰማሩ ይናገራል፡፡ “ከዚህ በኋላ ሰዎችን ታጠምዳላችሁ” (ማቴ. 4፡18-22) ተብለው፣ ለሦስት ዓመታት ለሐዋርያዊ ሥራ ሲዘጋጁ ቆይተው፣ የአፉን ትምሕርት ሰምተው የእጁነ ተዓምራት አይተው፣ ዛሬ እንደገና ወደ ጥንቱ ተግባራቸው ሲመለሱ እናያቸዋለን፣ ሰዎችን ሳይሆን ዓሣን ለማጥመድ ተሰማሩ፡፡ ነገር ግን ሌሊቱን ሙሉ ቢደክሙም ኢየሱስ ከነርሱ ጋር በታንኳው ላይ ስላልነበረ ምንም መያዝ አልቻሉም፣ ካለእርሱ ወጥተዋልና ባዶ እጃቸውን ተመለሱ፡፡ ጨለማው ሲያልፍና ንጋት ሲመጣ ግን የብርሃን አባትና የትንሣኤ ጌታ የሆነው ክርስቶስ በጥብርያዶስ ባሕር ተገለጠላቸው፡፡ እርሱ ሳይፈቅድ ምንም ነገር እንደማይሳካ ለማሳየትም ጭምር «መረቡን በታንኳው በስተቀኝ ጣሉ» አላቸው፤ እንደ ጨለማው ሰዓት ሳይሆን አሁን መረቧ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዘች፣ውጤታማ ሆነች - ክርሰቶስ አዝዞ የማይሆን ነገር የለምና፡፡
ይህ የወንጌል ክፍል ለዘመኑ ክርስቲያኖችስ ምን መልክት የስተላልፋል?
ከትምህርቱ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው፣ ያለ ክርስቶስ እገዛ ለራሳችን በራሳችን በቂ እንዳልሆንን የሚያመለክተው ነጥብ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ግን አንድ ልብ ልንለው የሚገባን ትምህርት አለ፡፡ ክርስቶስከሞት ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያቱ መቃብሩን ሊጎበኙ በመጡት ሴቶች በኩል መልዕክት ልኮባቸው ነበር “ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሔዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው” የሚል (ማቴ. 28፡10)፡፡ እዚያ እንዲጠብቁት፡፡ እግዚአብሔርን በመጠበቂያ ሥፍራ ላይ ሆኖ መጠበቅ፣ በትንቢተ ዕነባቆም እንደምናነበው “በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ በአምባ ላይም እወጣለሁ፣ የሚናገረኝንም ስለ ክብሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመላከታለሁ” (ዕን. 2፡1)፡፡
ሐዋርያቱ በተባሉት የቀጠሮ ስፍራ አልተገኙም በአንጻሩ ግን “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሰትና ጽድቁን ፈልጉ…” (ማቴ. 6፡33) የሚለውን ዘንግተውና በዓሣ ማጥመድ ችሎታቸው ተማምነው ወጡ፣ ውጤቱ ግን ባዶ ሆነ፡፡ ሁሉን መስጠት በሚችለው ክርስቶስ ማመንና መተማመን አማራጭ የሌለው ነው፡፡
እኛም በእምነት ጉዞአችን ወደኋላ የሚጎትተን ነገር አይጠፋም፡፡ ስንት ጊዜ የእግዚአብሔርን ምህረት ካገኘን በኋላ ወደ ቀድሞው ሥራችን ተመልሰን ይሆናል? ዛሬ ግን ያለፈውን አሰቃቂ ኑሮአችንን ወይም አስከፊውን ጊዜ እያሰቡ መተከዝና መቆዘም ሳይሆን ክርስቶስ በትንሣኤው ባመጣልን ብርሃን መመላለስ ነው፡፡ ስለዚህ የእምነት ጉዞአችን ያለ ክርስቶስ ባዶ ነው ልንገነዘበው ይገባል፤ እርሱ አብሮን በወጣ ጊዜ ግን ታሪክ ይቀየራል፤ እንደ ጴጥሮስና ጓደኞቹ በእምነትና በተስፋ መረቡን ወደ እግዚአብሔር የጸጋ ባሕር የጣለ ብዙ በረከትን ያጠምዳል፣ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ስጦታን ይቀበላል፡፡
ሰላም ወሠናይ
አባ ዳዊት ወርቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን
Share


ማን መሆናችን የዝግቶቹ ሰዓታት ለዝግጅት ክፍል ይጻፉ የቫቲካን ሬድዮ ክንውን ማገናኛዎች ሌሎች ቋንቋዎች የቫቲካን መታወቂያ ገጽ ሃገረ ቫቲካን የር.ሊ.ጳ. ሊጡርጊያውያን ሥርዓታት
የዚህ ድረገጽ ይዞታዎች ደራሲ መብት የተጠበቀ ነው ©. ድረ መስተዳድር / የደራሲያን ስሞች / ሕጋዊ ሁኔታዎች / ማታወቂያ