መታወቂያ ገጽየቫቲካን ሬድዮ
የቫቲካን ሬድዮ   
more languages  

     መታወቂያ ገጽ > ቤተ ክርስቲያን >  2013-06-14 18:53:40
A+ A- ገጹን ለማተም«ምስክሮቼ ትሆናላችሁ» (ሉቃ 24፡48፤ ሐዋ 1፡8)RealAudioMP3 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያቱ በተለያየ ጊዜ በመገለጥ ብዙ ነገሮችን አስተማራቸው፤ ቅዱሳን መጻሕፍትንም እንዲያስተውሉ አዕምሮአቸውን ከፈተላቸው (ሉቃ 24፡45)፡፡ ከዚያም የእርሱ ምስክሮች እንዲሆኑ ሐላፊነት ከሰጣቸው በኋላ ባረካቸው፣ እየባረካቸውም ሳለ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ (ሉቃ 24፡50-51)፡፡
በአዲስ ኪዳን ዘመን ስንኖር እግዚአብሔር በምድር ላይ ምን እንድናደርግ ነው የሚፈልገው? በዚህ ምድር እንጂ በሰማይ ማድረግ የማንችለውስ ነገር ምንድን ነው? በምድር ብቻ የምናደርገው ቢያንስ አንድ መሰረታዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ተግባር አለ፣ በጨለማ ለሚኖር ሁሉ መልካሙን ዜና መንገር፣ ብርሃንና የብርሃን ምንጭ የሆነውን ክርስቶስን ማስተዋወቅ፣ ስለ እርሱ በምድር ላይ ማወጅ፣ ስለ እግዚአብሔር አምላክነት፣ መሐሪነት፣ አፍቃሪነት ተስፋ ለቆረጠውና የሕይወት አቅጣጫን ለሳተው ትውልድ ይህን የመዳን ወንጌል ማወጅ፡፡ ይህን የመሰለ ተግባር ሁሉ በምድር ሳለን ልንወጣው የሚገባ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው - ድኖ ሌላው እንዲድን ማድረግ፡፡
በዘመናችን ይህን ዓይነት ስራ ለመስራት የሚያስፈልገው እስከ ዛሬ ድረስ በበቂ ሁኔታ ያልተጠቀምንበት የመንፈስ ቅዱሰ ኃይል ብቻ ነው፡፡ ይህ ብቻ ነው የሰውን ልብ መቀየርና ወደ መልካም መምራት የሚችለው፡፡ እንግዲህ መመስከር ሲባል እንደው ከመሬት ተነስቶ መናገር አይደለም፤ ከምንመሰክርለት ነገር ጋር በደንብ መተዋወቅ ያስፈልገናል፤ ቀምሰን ማጣጣም ያሻናል (መዝ 34፡8)፤ በመንፈስ መሞላትና መመራት ያስፈልጋል፤ የራስን ስሜት የምንገልጽበት መድረክ አይደለም የእግዚአብሔር ጉባዔ፤ የእርሱ መንፈስ የሚነግስበት እና የሚሰራበት እንጂ፣ ሰው ግን መሳሪያ ብቻ ነው፡፡
የሉቃስ ወንጌል “እየባረካቸው ሳለ ወደ ሰማይ ዐረገ” ይላል፡፡ ቤኔዲከቶስ 16ኛ ይህን ምስጢር እንዲህ ይገልጡታል “እነዚህ የክርስቶስ እጆች አሁንም ለቡራኬ እንደተዘረጉ ናቸው፤እነዚህ የሚባርኩ እጆች ልክ እንደ የቤት ጣሪያ ሆነው ከማንኛውም ክፉ ነገር ይጠብቁናል፤ የተዘጋውንም ዓለም በመክፈት የመንግስተ ሰማይ (የገነት) ማደሪያ ያደርጉታል፡፡”
የእግዚአብሔር አብ፣ የእግዚአብሔር ወልድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቡራኬ ከሁላችን ጋር ይሁን! አሜን!
ሠላም ወሰናይ

አባ ዳዊት ወረቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን
Share


ማን መሆናችን የዝግቶቹ ሰዓታት ለዝግጅት ክፍል ይጻፉ የቫቲካን ሬድዮ ክንውን ማገናኛዎች ሌሎች ቋንቋዎች የቫቲካን መታወቂያ ገጽ ሃገረ ቫቲካን የር.ሊ.ጳ. ሊጡርጊያውያን ሥርዓታት
የዚህ ድረገጽ ይዞታዎች ደራሲ መብት የተጠበቀ ነው ©. ድረ መስተዳድር / የደራሲያን ስሞች / ሕጋዊ ሁኔታዎች / ማታወቂያ