መታወቂያ ገጽየቫቲካን ሬድዮ
የቫቲካን ሬድዮ   
more languages  

     መታወቂያ ገጽ > ጕባኤ ኣስተምህሮን ጸሎት መልአከ እግዚአብሔርን >  2013-10-16 18:21:40
A+ A- ገጹን ለማተምሐዋርያነት;የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ
ውድ ወንድሞችና እኅቶች! መልካም ቀን ይሁንላችሁ! ጸሎተ ሃይማኖት በምንደግምበት ጊዜ፤ “አንዲት ቅድስት ካቶሊካዊትና እና ሐዋርያዊት በሆነችው ቤተ ክርስትያን አምናለሁ” እንላለን፣ ቤተ ክርስትያን ሐዋርያት ስለመሆንዋ አስተንትናችሁ የምታውቁ ከሆነ እኔ እንጃ! ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ሮማ በምትጐበኙበት ጊዜ የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያት አስፈላጊነት ታሰላስሉ ይሆናል ምክንያቱም እነኚሁ ታላላቅ ሓዋርያት ወንጌል እስከዚህ ለማድረስና ለመመስከር ሕይወታቸው ሰውተዋልና፣ ነገር ግን ሐዋርያነት ከዚህ በላይ ነው፣
ቤተ ክርስትያን ሐዋርያዊት ናት ብሎ መመስከር ከሓዋርያት ጋር ያላትን መሠረታዊ ትሥስርን ማስመር ነው፣ ይህ መተሳሰር ጌታ ኢየሱስ አንዴ ወደ ገዛ ራሱ የጠራቸው ትንሽ የአሥራ ሁለት ሰዎች ቡድን ማለት ሐዋርያት ብሎ የጠራቸውና ከእርሱም እንደተቀመጡ እርሱም ወንጌልን ለመስበክ እንደላካቸው በወንጌለ ማርቆስ 3፡13 ላይ እናነባለን፣ ሐዋርያ የሚለው ቃል ከግሪክ የተወሰደ ሲሆን አፖስቶሎ ማለት የተላከ ማለት ነው፣ ሐዋርያ ማለት አንድ ነገር ለማድረግ የተላከ ማለት ነው፣ ኃይለኛ ቃል ነው፣ ሐዋርያት መጀመርያ በጌታ ኢየሱስ ተመረጡ ከዛም ተጠሩ በመጨረሻም የእርሱን ተግባር ለመቀጠል ተላኩ፤ ማለትም ለመጸለይ! ጸሎት የአንድ ሐዋርያ የመጀመርያ ሥራ ነው፣ ሁለተኛው የሐዋርያ የጸሎት ሥራም ወንጌልን ማብሰር ነው፣ ይህም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ሐዋርያትን ብምናስብበት ግዜ ወንጌልን ለመስበክና ሌላ ብዙ ሥራዎች ለማድረግ የተላጉ እነርሱ ብቻ ሆኖ ይሰማናል ነገር በቤተ ክርስትያን የመጀመርያዎቹ ዘመናት አንድ ችግር ተፈጠረ፤ ብዙ ነገሮች ባንድነት ያደርጉ ነበር አንዳንዴ ግን ሁሉንም ለማድረግ ጊዜ አያገኙም ነበር፣ ስለዚህ ለጸሎትና ለስብከተ ወንጌል በቂ ጊዜ እንዲያገኙ ለማለት ሰባት ዲያቆናት በመምረጥ አንዱን የሥራ ክፍል ለዲያቆናት ትተዋል፣ የሐዋርያት ተከታዮች ማለትም ስለ ጳጳሳት ያሰብንም እንደሆነ ማለት ሁሉም ጳጳሳት ር.ሊ.ጳጳሳትም ጳጳስ ነው! እነኚህ የሐዋርያት ተከታዮች ከሁሉ አስቀድሞው ይጸልያሉን ወንጌልንስ ይሰብካሉን ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል፣ ሐዋርያ መሆን ማለት ይህ ነው ለዚህም ነው ቤተ ክርስትያን ሐዋርያዊት የምንላት፣ እኛ ሁላችን ሐዋርያት ለመሆን ከፈለግን ቆየት ብየ እንደምገልጥላችሁ “ስለ የዓለም ደህንነት እጸልያለሁን ወንጌልንስ እሰብካለሁን” ብለን ለገዛ ራሳችን እንጠይቅ፣ ሐዋርያት የምንላት ቤተ ክርስትያን ይህች ናት፣ ከሐዋርያት ጋር ያለን መተሳሰር ገንቢና መሠረታዊ ነውና፣
ከዚህ በመነሳት ስለዚሁ ሐዋርያዊት የሚለው ለቤተ ክርስትያን የሚገልጽ ቅጽል አጠር ባለ መንገድ ሶስት ሐሳቦች ለማስመርና ለመግለጥ እወዳለሁ፣
1ኛ ቤተ ክርስትያን ሐዋርያዊት ናት ምክንያቱም በሐዋርያት ስብከትና ጸሎት እንዲሁም በእርሳቸው ሥልጣን ስለተመሠረተችና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ስለሰጣቸው፣ ቅዱስ ጳውሎስ በኤፈውሶን ወደ ነበሩ ክርስትያኖች ሲጽፍ “ስለዚህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጐችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ እንግዶችና መሳተኞች አይደላችሁም፣ በሐዋርያትና በነቢያትም መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑም ራስ የሆነው ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (2፤19-20) በማለት ክርስትያኖችን እንደሕያው ድንጋዮች ሆነው ቤተ ክርስትያንን እንደሚያቆሙ የሕንጻው አዕማድና መሠረትም ሐዋርያት መሆናቸውን ሁሉንም አጥንቶ የሚይዝም የማእዝን ድንጋይ የሆነው ኢየሱስ ራሱ መሆኑን ይገልጣል፣ ኢየሱስ ከሌለ ቤተ ክርስትያን ለመኖር አትችልም ይህንን ትረዳላችሁ ወይ! ኢየሱስ የቤተ ክርስትያን መሠረት ነው፣ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር ኖረዋል፤ ቃላቶቹን ሰምተዋል፤ ሕይወቱን ተካፍለዋል ከሁሉ በላይ ደግሞ የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆነዋል፣ እምነታችን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ የተመኛት ቤተ ክርስትያንችን በአንድ ሓሳብ ወይንም በአንድ ፍልስፍና አትመሠረትም በኢየሱስ ክርስቶስ ነው የምትመሠረተው፣ ይህች ቤተ ክርስትያንም በዘመናት ጋር ያደገች የበለጸገችና ፍሬ የሰጠች ተክል ናት ሆኖም ግን ስሮችዋ በኢየሱስ ክርስቶስ ጠብቀው በጌታ ኢየሱስ ተመርጠው እስከ እኛ ድረስ የተላኩ ሐአርያት ያጣጣሙት መሠረታውያን የኢየሱስ ክርስቶስ ነገሮችን በማጣጣምም ነው፣ ከዚች ያኔ እጅግ ታናሽ የነበረች ተክል ይህች ታላቅ ተክል ተገኘ ቤተ ክርስትያንም ለመላው ዓለም እንዲሁ ናት፣
2ኛ ከዛኛው ምስክርነት እኛ እንዴት አድርገን መተሳሰር እንችላለን? ያ ሐዋርያት ከኢየሱስ የሰሙትና ከእርሱ ጋር የኖሩት እንዴት ሆኖ ወደ እኛ ሊደርስ ይችላል? ብለን የጠየቅን እንደሆነ፤ ሁለተኛው የሐዋርያነት ትርጉም እዚህ እናገኘዋለን፣ አዲሱ የካቶሊካዊት ቤት ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ በቍጥር 857 ላይ “ቤተ ክርስትያን ሐዋርያዊት ናት፤ ምክንያቱም በሶስት መንገዶች በሐዋርያት ላይ ተመሥርታለችና፤ በሐዋርያት ክርስቶስ ራሱ በመረጣቸውና በላካቸው ምስክሮች የተሰረተች አሁንም በዚያ የጸናች ናት፣ በውስጧ ባደረው መንፈስ ቅዱስ ረዳነት ቤተ ክርስትይን ትምህርቱን ከሐዋርያት የሰማችውን የሰላምታ ቃል መልካሙን ሃብት ጠብቃ በማቆየት ታስተላልፋለች፣” ይላል፣ ቤተ ክርስትያን ለረዥም ዘመናት ይህንን ክቡር መዝገብ ማለትም ቅዱስ መጽሓፍ መዝገበ ሃይማኖት ምስጢራትንና የእረኞች ተልእኮን ይዛ ትገኛለች በዚህም የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮችና በመሆን በሕይወቱ ለመሳተፍ እንችላለን፣ ቤተ ክርስትያን በታሪክዋ ብዙ ነገር ይዞ እንደሚጓዝ ወንዝ ናት፤ ልክ ወንዙ በየጊዜው እያደገና በአከባቢው ያለውን ቦታ እያለማ እንደሚጓዘው ቤተ ክርስትያንም እንደዛው ናት፣ በቤተ ክርስትያኑ ወንዝ የሚጐርፈው ውኃ ግን ከአንድ ምንጭ ብቻ ነው የሚፈልቀው፤ ምንጩም ከሙታን ተለይቶ የተነሳው ሕያው የሆነውና እርሱ ስለማያልፍም ቃሉ የማያልፍ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣ እርሱ ሕያው ነው፣ አሁን በመካከላችን ይገኛል! ከእርሱ ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ ይሰማናል! እርሱ ዘወትር ያዳምጠናል! እርሱ በልባችን ውስጥ ይገኛል፣ ዛሬ ኢየሱስ ከእኛ ጋር አለ! የቤተ ክርስትያን ደስ የሚያሰኝ ነገር ደግሞ ይህ ነው! የኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን ለዘላለም መኖር፣ ኢየሱስ ሕያው ነውና ማለትም ከሙታን ተለይቶ ተነስተዋልና ለማለት ነው፣ ይህ ኢየሱስ ያደረገልን ታላቅ ስጦታ ማለት የቤተ ክርስትያን ስጦታ ምንኛ ያህል አስፈላጊ መሆኑን እናስታውሳለንን? ከችግሮቻችን ከድካሞቻችንና ከኃጢአቶቻችን ባሻገር ይህች ቤተ ክርስትያን የክርስቶስ ትክክለኛ መል እክትን እንደምታስተላልፍን እናስታውሳለንን? የምናምነው በእውነት ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተላለፈልን መሆኑን እርግጠኝነት የምትሰጠን ቤተ ክርስትያን መሆንዋንስ እናስታውሳለንን?፡
3ኛና የመጨረሻው ሃሳብ፤ ወንጌልን ለመላው ዓለም ለመስበክ የተላከች በመሆንዋ ቤተ ክርስትያን ሐዋርያዊት ናት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት አደራ የሰጠውን መል እክት ለማስተላለፍ ቤተ ክርስትያን በሰው ልጆች ታሪክ ጉዞ ውስጥ ትጓዛለች፣ ኢየሱስ ምን አለ? ብለን የጠየቅን እንደሆነ በወንጌል ማቴዎስ 28፤19 ላይ “እንግዲህ ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ፤ በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠቃችኋቸው የእኔ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲፈጽሙ አስተምሯቸው፣ እነሆ እኔ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነን” የሚል መልስ እናገኛለን፣ ስለዚህ ኢየሱስ ያዘዘን ይህ ነው፣ በዚሁ የስብከተ ወንጌል ተል እኮ ደጋግሜ መናገር እወዳለሁ ምክንያቱም ክርስቶስ ሁላችንን ነው ወንጌል ለመስበክ ሂዱ ብሎ ጥሪ የሚያቀርብልን፣ የዚህ ዜና ሠናየ ምሥራች ለሊሎች ለማዳረስ ተነቃነቁ ብሎ ዘወትር እየጠራን ነው፣
እስቲ አሁንም እንደገና መለስ ብለን፤ በንግግራችን ሰባክ ያነ ወንጌል ነንን? ከሁሉ በላይ ደግሞ በክርስትያናዊ ሕይወታችን የወንጌል ሰባኪዎች ነንን? በምንሰጠው ምስክርነታችንስ? ወይስ የሳክርስቲ ክርስትያኖች በመሆን በገዛ ራሳችንና በቤተ ክርስትያኖቻችን የተዘጋን ነን? ወይስ የቃል ክርስትያኖች ሆነን በተግባር ግን እንደ አረማውያን የምንኖር ክርስትያኖች ነን? ይህን አስተንትኖ የግድ ማድረግ አለብን፣ ምናልባት የምከሳችሁ ወይንም የምወቅሳችሁ እንዳይመስላችሁ እኔም ክርስትያን እንደመሆኔ መጠን ለገዛ ራሴ ክርስትያንነቴን በእውነት በሕይወትየ እመሰክረዋለሁን ብየ እጠይቃለሁ፣
ቤተ ክርስትያን ሥሮችዋ ታማኝ ምስክሮች በሆኑ በሐዋርያት ትምህርት አኑራለች፤ ሆኖም ግን ሁልጊዜ ወደፊት ወደመጻኢ በማትኰር በኢየሱስ ክርስቶስ እንድትላክ በጽኑ ኅልና እየተጠባበቀች ነው፣ ይህንን የምታደርገው ደግሞ ዘወትር የኢየሱስ ክርስቶስ ስምን በመመርኰዝ በጸሎትና ወንጌልን ለሁሉ ሰው በመስበክ ነው፣ እንዲሁም ምስክርነትዋን በተግባር እየሰጠች ነው፣ በገዛ ራስዋ ተዘግታ በታሪክ ብቻ የምትኖር ቤተ ክርስትያን ወይንም ጥቃቅን በሆኑ ሕጎችና ዝንባሌዎች ብቻ ታጥራ የምትቀር ቤተ ክርስትያን ማንነትዋን የከዳች ቤተ ክርስትያን ናት፣ ስለዚህ ዛሬ ሐዋርያዊ መሆን ማለት መጀመርያ በጸሎት ሁለተኛ ደግሞ በስብከተ ወንጌል ይህንን ደግሞ በተግባርና በሕይወት በመመስከር መሆን አለበት፣ በንግግራችንም መስበክ አለብን፣ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፣
Share


ማን መሆናችን የዝግቶቹ ሰዓታት ለዝግጅት ክፍል ይጻፉ የቫቲካን ሬድዮ ክንውን ማገናኛዎች ሌሎች ቋንቋዎች የቫቲካን መታወቂያ ገጽ ሃገረ ቫቲካን የር.ሊ.ጳ. ሊጡርጊያውያን ሥርዓታት
የዚህ ድረገጽ ይዞታዎች ደራሲ መብት የተጠበቀ ነው ©. ድረ መስተዳድር / የደራሲያን ስሞች / ሕጋዊ ሁኔታዎች / ማታወቂያ