መታወቂያ ገጽየቫቲካን ሬድዮ
የቫቲካን ሬድዮ   
more languages  

     መታወቂያ ገጽ > ቤተ ክርስቲያን >  2014-03-27 19:02:55
A+ A- ገጹን ለማተምየዐቢይ ዖም ስድሰተኛ ሰንበት - «ገብርኄር»RealAudioMP3 በዛሬው የወንጌል ንባብ (ማቴ. 25፡14-30) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደግ እና የሰነፍ አገልጋይ ተግባርና የመጨረሻ ዕጣ ክፍል ምን እንደሚሆን ያስተምረናል፡፡ በዚህ ወንጌል ክርስቶስ የእግዚአብሔርን መንግስት ከአንድ አገልጋዮቹን ጠርቶ ለሦስቱም እንደየአቅማቸው ይሰሩበት ዘንድ ንብረቱን አከፋፍሎና፣ለአንዱ አምስት፣ለሌላው ሁለት፣ለሦስተኛው ደግሞ አንድ፣በአደራ ሰጥቶ ከሄደ ሰው ጋር ያነጻጽራታል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የተሰጣቸውን ሰርተውበት፣እጥፍ አግኝተውበት ወደ ጌታቸው ሲቀርቡ የመጨረሻው ደግሞ የተሰጠችውን ምንም ሳይነካት እንዳለች የወቀሳና ጌታውን (ሰጪውን) ከሚዘልፍ ንግግር ጋር ቀረበ፡፡ የነዚህ ሰዎች መጨረሻ እንደየ ስራቸው የተለያየ ሆነ፤በትንሽ ታማኝ ሆነው የተገኙት ጌታቸው በብዙ ላይ ሾማቸው፣በሁሉ ነገር ላይ አሰለጠናቸው፣ከዚያም አልፎ የጌታቸውን ደስታ ለመካፈል በክብር እንዲገቡ፣አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲራመዱ አደረጋቸው፣በሰው እና በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አገኙ፡፡ የሦስተኛው ሰው ዕጣ ክፍል ግን ከነዚህኞቹ የተለየ ሆነ፤ ምክንያቱም አስተሳሰቡም ሆነ አነጋገሩ ከእግዚአብሔር አሰራር ጋር የሚሄድ አልነበረም፡፡ ሰርቶ ከመሞከር ይልቅ ገና ምኑንም ሳይዘው፣መስራት ሳይጀምር «ስሰራ እንዲህ ቢሆንብኝስ፣ብሰረቅስ፣ብከስርስ፣ባይሳካልኝስ…» በሚል ስጋት ተሞልቶ እጁን አጣምሮ መቀመጥን የመረጠ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ሲያተርፍ ሳይሆን ሲከስር፣እጥፍ ሲያደርግ ሳይሆን ያለውን ሲቀማ እየታየው ጭራሽ ሳይተኛ ነበር የሚያድረው፡፡ ሌላው የሚገርመው ነገር ደግሞ ለጌታው መልስ የሰጠበት ሁኔታ ነው፤ አነጋገሩ፣የተጠቀመው ቋንቋ «ጨካኝ፣ክፉ…» የሚል ነበር፡፡ ይህ አገልጋይ ቃሉ መራራ ነው፣ ስንፍናው ያለመስራት ወይም የአካል ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡም፣አነጋገሩም፣አዕምሮውም ጭምር ነው ሰነፍ የነበረው፡፡እስቲ ወደራሳችን ደግሞ እንምጣ፡፡ ስጦታችን ምንድን ነው? እግዚአብሔርስ ምንድን ነው በእቅፋችን የሰጠን፣እጃችን ላይ ያስቀመጠው? ሮሜ ም.12 ከቁ.6 ጀምሮ ያለውን ስናነብ ቅ. ጳውሎስ እነዚህን ስጦታዎች ይዘረዝራል፡ ትንቢት የመናገር፣የማገልገል፣የማስተማር…ወዘተ፡፡ እንዲሁም በ1ቆሮ ም.12 ከቁ.7 ጀምሮ ደግሞ ሐዋርያው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን ተንትኖ ሲያስቀምጣቸው እነዚህ ስጦታዎች ለሌሎች አገልግሎት ጭምር መሆኑንም አስምሮበት ነው፡፡
እንደ ሦስቱ አገልጋዮች ሁሉ በቤተ-ክርስቲያናችንም ውስጥ እንዲሁ የተለያየ ስጦታ የተሰጣቸው አሉ፡፡ ይነስም ይብዛ እግዚአብሔር አንድ ነገር ሰጥቶናል፡፡ ለመስራት ወይም ለማትረፍ ከመውጣታችን በፊት ግን ምን ዓይነት መክሊት እንደተቀበልን ወደ ውስጣችን እንመልከት እና እንወቀው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የሚባክን ጊዜ የለምና ለሥራ እንሰማራ፣ ይህ የእግዚአብሔር አደራ ነውና፡፡ ይህ መክሊት የክርስቶስ የአካል ክፍል ለሆነ ሁሉ ተሰጥቷል፤ የአካል ክፍል ደግሞ የራሱ የሆነ ተግባር አለው፤ የክርሰቶስ እግሩ ከሆንክ እርሱ ወደሚልክህ ሂድ (ወደ ወገኖቹ፣ወደ ተገፉት፣መዳን ወደሚያስፈልጋቸው፣ ተስፋ ወደቆረጡት፣መጽናናትን ወደሚሹት አቅና)፤ የክርሰቶስ ዓይን ከሆንክ ወደ በጎ ተመልከት፣የበደለህም ካለ በምህረት ተመልከተው፤ የክርስቶስ ምላስ (አንደበት) ከሆንክ ደግሞ ስጦታህ ነውና መልካም ዜናን፣ፍቅርን፣ሰላምን፣ዕርቅን ዓውጅበት፡፡
ገበሬ ሲዘራ እጁ ላይ ያለውን ጥቂት ዘር በእምነት ነው የሚዘራው፤ ጎርፍ ይወስደዋል፣ወፍ ይበላዋል፣ፀሓይ ያደርቀዋል ሳይል ለመሬት በእምነት ለመሬት ያበድራል፣መሬትም አደራዋን ሳትበላ በብዙ እጥፍ ትሰጠዋለች፤ የእግዚአብሔርም መክሊት (ጸጋ) እንዲሁ ነው፡፡ በአቅማችን የተወሰነ ብቻ ይሰጠናል፣ በዚያች ያተረፍን እንደሆነ ደግሞ መልሶ በዘለዓለማዊ ደስታ የምንኖርበትን መንግስተ ሰማይን ርስተ አድርጎ ይሸልመናል። ስለዚህ የተሰጠንን መክሊት ይዘን በእምነት እንሰማራ፣ስንወጣም እግዚአብሔርን ራሱን ይዘን እንውጣ፤ መታበይን ወይም በተሰጠን ስጦታ መኩራራትን እናስወግድ የክርስቲያን ባህሪ አይደለምና፤ ካልሆነ ግን እግዚአብሔር የሰው ድሀ ስላልሆነ ሌላውንና እሱ የፈቀደውን ያስነሳል፣የሚሰራ ሰው ይጠራል በወንጌል «እግዚአብሔር ከፈቀደ ለአብርሃም ከነዚህ ድንጋዮች ልጆች ሊያስነሳለት ይችላል» እንደተባለው (ማቴ 3፡9)። ስለዚህ ቀናችን ሳይጨልም፣ጉልበታችን ሳይልም በተሰጠን መክሊት እንስራበት፤ ለቃሉ ታማኝ የሆነውም አምላካችን የድካማችንን ዋጋ ካተረፍነው አብልጦ ይሰጠናል።

የእግዚአብሔር አብ፣የእግዚአብሔር ወልድ፣የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቡራኬ ከሁላችሁ ጋር ይሁን! አሜን!
ሠላም ወሰናይ!አባ ዳዊት ወርቁ
ዘማኅበረ ካፑቺን
Share


ማን መሆናችን የዝግቶቹ ሰዓታት ለዝግጅት ክፍል ይጻፉ የቫቲካን ሬድዮ ክንውን ማገናኛዎች ሌሎች ቋንቋዎች የቫቲካን መታወቂያ ገጽ ሃገረ ቫቲካን የር.ሊ.ጳ. ሊጡርጊያውያን ሥርዓታት
የዚህ ድረገጽ ይዞታዎች ደራሲ መብት የተጠበቀ ነው ©. ድረ መስተዳድር / የደራሲያን ስሞች / ሕጋዊ ሁኔታዎች / ማታወቂያ