2009-05-13 15:46:59

ሐዋርያዊ ዑደት ር.ሊ.ጳ. በነዲክቶስ 16ኛ በመካከለኛው ምሥራቅ በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ ነው


ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በመካከለኛው ምሥራቅ የጀመሩት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ሲል በወጣው መርኃ ዑደት መሠረት እየተካሄደ መሆኑ የቫቲካን እና የእስራኤል መገናኛ ብዙኀን ያመለክታሉ። RealAudioMP3

በመገናኛ ብዙኀኑ መሠረት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በትናትና የቅዱሳን ስፍራዎች ጉብኝታቸው፤ ኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኘው በመካ መዲና ከሚገኘው መስጊድ በኋላ ጥንታዊ እና ታሪካዊ የሆነ የአለት ጉልላት ባለበት መስጊድ፡ የእብራውያን የሕይወት ማእከል መሆኑ የሚነገርለት የልቅሶ ግድግዳ፡ እና ኢየሱስ ክርስቶስ በስቅላት ከመሞቱ በፊት ከሐዋርያቱ ጋር ለመጨረሻ እራት የተቀመጠበት እና ከትንሳኤው በኋላ ሐዋርያቱ የተገናኙበት ማለትም ምሥጢረ ቅዱስ ቁርባን እና ምሥጢረ ንስሐ የተሠራበት ወይም ጽርሓ ጽዮንም ጐብኝተዋል።

ይሁን እና ቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ መገናኛ ብዙኀን እንደገለጡት፡ ትልቁ ጥንታዊውና ታሪካዊው የአለት ጉልላት መስጊድ ሲገቡ እንደ እስላሞች ወግ እና ባህል ጫማቸው አውጥተው ገብተዋል።

ዐቢይ የመስጊዱ ሙፍቲ፣ እስራኤል ፍልስጤማውያንን በቅዱሳን ስፍራዎች በነጻ የመንቀሳቀስ ነጻነታቸው እንደምትገድብ ለርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት እንደገለጡላቸው የተመለከተ ሲሆን የሮማዊት እንተላዕለ ኩሉ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት፡ በመስጊዱ ላይ የተሰቀለው የአለት ጉልላት፡ የፍጥረት ምሥጢር እና የአብርሃም እምነት የሚያሳስብ መሆኑ ጠቅሰው፡ እዚህ ላይ ነው የሶስቱ ዐበይት ሃይማኖቶች ማለት ክርስትና እስላም እና አይሁዳዊ እምነት የሚገናኙት በማለት መግለጣቸው ተነግረዋል።

አያይዘው ይህ የተቀደሰ ስፍራ በሚያሳዝን መልኩ የተከፋፈለች ዓለም ያለፉትን ግጭቶች እና መከፋፈል ለመፈወስ ፍትሓዊት እና ሰላማዊት ዓለም ለመገንባት ሕንፀተ ሰላም ለማካሄድ ችሎታ ያለው ቅዱስ ቦታ መሆኑ ማስገንዘባቸው ተመለክተዋል።

የሰው ልጆች ህልውና የሚመነጨው ከአንድ ብቸኛ እግዚአብሔር መሆኑ ያሰመሩበት ር.ሊ.ጳ በነዲክቶስ እምነታቸው በሱ ብቻ መሆን እንደሚገባ ማስገንዘባቸው ተገልጠዋል።

ሦስቱ የተጠቀሱት ሃይማኖቶች መከፋፈል እና አለመጣጣም ገትተው በሰው ልጅ መሀከል ትብብር ፍቅር እና መፈቃቀድ እንዲኖር አቢይ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።

የሰው ልጅን ከጥላቻ ከቁጣ ከመበቀል ከእኩይ ተግባሮች ሁሉ ማላቀቅ እንደሚጠበቅባቸው ማሳሳሰባቸውም ታውቆዋል።

ቅዱሱ አባታችን ከየኢየሩሳሌም ዐቢይ መስጊድ ወጥተው የሄሮድስ ቤተ መቅደስ ድንጋዮች ወደ ሚገኝበት የአይሁድ ቅዱስ ስፍራ እና የእምነታቸው እምብርት ወደ ሆነው እና የልቅሶ ግድግዳ መጓዛቸው፡ እና እቦታው የረበናት የበላይ ሓላፊ እንደተቀበልዋቸው እና ከመዝሙረ ዳዊት በላቲን እና በእብራይስጥ ለኢየሩሳሌም ሰላም በጋራ መጸለያቸው ታውቆዋል። ከዚያም በየልቅሶ ግድግዳ ቀዳዳ አንድ መልእክት ጽፈው ማስቀመጣቸው ተመልክተዋል፡

ኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኙ የቫቲካን እና የአከባቢው መገናኛ ብዙኀን እንዳመለከቱት፡ የመልእክቱ ይዘት ‘‘ኦ ዘለዓለማዊ እግዚአብሔር ሆይ በኢየሩሳሌም የሰላም ከተማ ጉብኝቴ በዚህ የክርስትያን እብራውያን እና እስላም መንፈሳዊ ቦታ፣ የሰው ልጅ ዘር ሁሉ ደስታዎች ተስፋዎች ፍራቻዎች እና ስቃዮች አቀርብልሃለሁ። የአብርሃም የይስሓቅ እና የኢዮብ እግዚአብሔር ሆይ! ፍርሃት ያሸነፋቸው፤ ተስፋ የቁረጡ እና የሚሰቃዩ ሕዝቦችህ እሮሮ አዳምጥ፡ ለዚች ለተቀደሰች መሬት ለመካከለኛው ምሥራቅ እና ለመላው ዓለም ሕዝቦች ሰላምህ አውርድ፡ ስምህ ለሚጠሩ ሁሉ ልባቸው ክፈትላቸው፣ ራራላቸው፣ በትሕትና የፍትሕ እና የምሕረት መንገድ እንዲራመዱ አድርግ’’ የሚል መልእክት ነበር።

ከዚህ በኋላም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ ሄሻል ሻልሞ በተባለ የእስራኤል የዐቢይ ራቢን መኖርያ ከራቢኑ ጋር የተወያያዩ ሲሆን፡ በዓለም ዙርያ ጥላቻ እና ማሳደድ ሁለቱ ወገኖች በጋራ ለመታገል በሚያስችላቸው ሁኔታ መወያየታቸው እና በሁለቱ መሀከል የተካሄዱ ውይይቶች ስኬታማ መኖራቸው መገናኛ ብዙኀኑ አስታቀዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እንድገለጹት፤ ክርስትያን እና ዕብራውያን የሰው ሕይወት ቅሱስነት፣ የቤተሰብ ማእከልነት፣ የሃይማኖት ነጻነት፣ እንዲረጋገጥ ይሻሉ በማለት ከውይይቱ በኋላ መግለጫ መስጠታቸው ተያይዞ ተነግረዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅድስት መሬት እያካሄዱት ያሉት ጉብኝት የቀድሞዎቹ አርእስተ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እና ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በኢየሩሳሌም ያደረጉት ጉብኝት መስመር የተከተለ ነው።

RealAudioMP3







All the contents on this site are copyrighted ©.